Wednesday, November 11, 2009

ኢትዮጵያ የዐጀሚ ሥነ ጽሑፍ ሀገር

Sunday, 08 November 2009
በሔኖክ ያሬድኢትዮጵያ፣ ሥነ ጽሑፋዊ ቅርሶቻቸውን በዐረብኛ ፊደላት እየጻፉ ያስተላለፉ 11 ቋንቋዎች ያሏትና በዚህም፣ በአፍሪካ በተጠቃሚ ቋንቋዎች ብዛት የመጀመሪያውን ደረጃ መያዟ አንድ ጥናት አመለከተ፡፡
ጥቅምት 26 ቀን 2002 ዓ.ም. በተጠናቀቀው 17ኛው የኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባኤ በሦስተኛው ቀን ውሎው፣ “ኢትዮጵያ አንጋፋዋ የአፍሪካ የዐጀሚ ሥነ ጽሑፍ ሀገር” በሚል ርእስ ጥናት ያቀረቡት፣ አቶ ሙሐመድ ሰዒድ አብደላ እንዳመለከቱት፣ ሀገር በቀል በሆኑት የኢስላም ሃይማኖት ተቋማት የተማሩና ከፍተኛ የዕውቀት ደረጃ ላይ የደረሱ ኢትዮጵያውያን፣ አንዳንዶቹ በዐረብኛ ቋንቋ፣ ከፊሎቹ ደግሞ በአማርኛና በሌሎች የሀገሪቱ ቋንቋዎች የዐረብኛ ፊደሎችን በመጠቀም ድርሳኖችን እየጻፉ፣ ሥነ ጽሑፋዊ ቅርሳቸውን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲያስተላልፉ ኑረዋል፡፡ ዐረብኛ ያልሆኑና በዐረብኛ ፊደላት ሲጻፉ የቆዩ ቋንቋዎች፣ ያፈሯቸው የጽሑፍ ቅርሶች፣ ዐጀሚ ተብለው እንደሚጠሩ የጠቀሱት አቶ ሙሐመድ፣ የአጻጻፍ ስልቱ የአፍሪካና የእስያ ሕዝቦች፣ ቋንቋቸውን በዐረብኛ ፊደል በመጠቀም የታሪካቸው፣ የባህላቸውና የሥነ ጽሑፋቸው መግለጫ መሣሪያ በመሆን አገልግሏል፡፡ በኢትዮጵያ የዐጀሚ ጽሑፍ ታሪካዊ መነሻን የሚገልጽ መረጃ ለጊዜው ባይገኝም፣ በእጅ የሚገኙት መዛግብት ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተጻፉ መሆናቸው አጥኚው አመልክተዋል፡፡ በሀገሪቱ፣ በዐጀሚ የጽሑፍ ቅርስ በብዛት የተገኙት፣ በሴሜቲክና በኩሽቲክ ቋንቋዎች የተጻፉና ይዘታቸውም በአብዛኛው በሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ በአቶ ሙሐመድ ማብራሪያ፣ እስከ አሁን ድረስ በኅብረተሰቡ ውስጥ በብዛት የሚታወቀውና በተለያዩ ቋንቋዎች ለሕዝብ የሚደርሰው መንዙማ፣ ሥነ ጽሑፋዊ ይዘቱ በዐረብኛ ፊደል የተጻፈና በከፊልም ቢሆን በአማርኛና በሌሎች ሀገርኛ ቋንቋዎች የተደረሰ ነው፡፡ ብዙዎቹ የመንዙማ ጽሑፎች በኢትዮጵያውያን የእስልምና ሃይማኖት ሊቃውንት የተደረሱት ከምእት ዓመታት በፊት ነበር፡፡ አጥኚው ባቀረቧቸው የሰነድ መረጃዎች፣ በዐጀሚ ከተጻፉት የሴሜቲክ ቋንቋዎች አማርኛና ትግርኛ፣ ሐደርኛና አርጎብኛ፣ ስልጥኛና ወለንኛ፣ ከኩሽቲክ ቋንቋዎች ደግሞ አፋን ኦሮሞ፣ አፋርኛና አላባ፣ ቀቤንኛና ሶማልኛ ይገኙባቸዋል፡፡ የዐጀሚ ጽሑፍ የተጻፈባቸው አስራ አንድ ሀገር በቀል ቋንቋዎች መገኘታቸው ያመለከቱት አቶ ሙሐመድ፣ የሥነ ጽሑፉ ቅርስ ከሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ጉዳዮች ጎን የተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮችን፣ የንግድ ግንኙነትን፣ የጋብቻ ሥርዓትን፣ የሕዝብ አስተዳደርን፣ የንብረት ዝውውርንና የመሬት ይዞታን ወዘተ. በብዛት እንደሚዳስስ አስረድተዋል፡፡ የኢትዮጵያ የዐጀሚ ሥነ ጽሑፍ ቅርስ፣ ለረዥም ዘመናት አትኩሮት ሳያገኝ በመቅረቱ፣ ትውልዱም ስለሁኔታው ያለው ዕውቀት ውስን ቢሆንም፣ ያላት ቅርስ ከአፍሪካ ሀገሮች ቀደምት ቦታ የሚያሰጣት መሆኑን ከአፍሪካ ሀገሮች ቅርስ ጋር በማነፃፀርም አብራርተውታል፡፡ በሰሜን አፍሪካ የሚኖሩ ዐረብኛ ተናገሪ ሀገሮች፣ እስካሁን ድረስ የቅድመ ዐረብኛ የጽሑፍ ቅርስ በብዛት ስለመኖሩ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ በምዕራብ አፍሪካ ያለውን ሁኔታም ወደ አስር የሚሆኑ ቋንቋዎች በቡርኪናፋሶ፣ በጋምቢያና በጊኒ፣ በሴኔጋልና በማሊ፣ በኒጀርና ናይጄሪያ የሚነገሩ በዐጀሚ የተጻፉ መኖራቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እስልምና ከነቢዩ ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያ የሚገኝ መሆኑ፣ ሃይማኖቱን የተቀበሉ ኢትዮጵያውያን ከሰሜን አፍሪካ ሕዝቦች በተለየ ሁኔታ ከቅድመ እስልምና ዘመን ጀምሮ ይዘዋቸው የቆዩትን ቋንቋዎች እስከ አሁን እንደያዙ ቀጥለዋል፡፡ ሃይማኖቱን ለመማርና ለማስተማር በስፋት የተገለገሉት ሀገር በቀል በሆኑት ቋንቋዎች ሲሆን፣ ለመጻፍም በዐረብኛ ፊደል ሲጠቀሙ ኖረዋል፡፡ ከቋንቋ ስርጭት አኳያም፣ ኢትዮጵያ ከስዋሂሊኛ በስተቀር በአፍሪካ ቀንድ የሚነገሩት ቋንቋዎች የሚነገሩባት በመሆኗ፣ አሁን ባለው መረጃም በሀገር በቀል ቋንቋዎች በዐጀሚ ተጽፈው መገኘታቸው ከአፍሪካ ጎልታ እንድትታይ አድርጓታል፡፡ በአቶ ሙሐመድ አገላለጽ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዐረብኛ ተናጋሪ ከሆኑት የግብፅ የሃይማኖቱ ተከታዮችና ተቋሞቻቸው ጋር በነበራት ታሪካዊ ግንኙነት ጥንታዊ የክርስትና ሃይማኖት የጽሑፍ ቅርሶች ከዐረብኛ ወደ ግእዝ፣ አማርኛና ትግርኛ እየተተረጎሙ፣ ለሕዝብ አገልግሎት የመድረሳቸው ድምር ውጤት፣ ዛሬ በኩራት የምንጠቅሰውን ሰፊና ጥንታዊ የኢትዮጵያ ዐጀሚ ሥነ ጽሑፍ ቅርስ ለማፍራት አብቅቷል፡፡ ኢትዮጵያ፣ ከአፍሪካ አንጋፋዋ ዘርፈ ብዙ የዐጀሚ ሥነ ጽሑፍ ቅርስ ባለቤት በመሆኗ፣ ከመቶዎች ዓመታት በፊት የነበረውን የሕዝቦቿን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ጉዳዮችን ለማጥናት ጽሑፉ እንደ መጀመሪያ ምንጭ ሊሆን ስለሚችል፣ የሀገሪቱ ትምህርትና የምርምር ተቋማት የሚገባውን ግምትና አትኩሮት እንዲሰጡበት አጥኚው ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡ “የኢትዮጵያ የዐጀሚ የጽሑፍ ቅርስን በምርምር እና በጥናት ታሪካዊ ዋጋው ግምት አግኝቶ ለማኅበረሰቡ ጥቅም የሚውልበት ሁኔታ ለማመልከት በኅብረተሰቡ ተጠብቆ የቆየውን ሀገር በቀል የሃይማኖትና የሥነ ምግባር የባህልና የሥነ ጽሑፍ ቅርስ በሚገባ ለማወቅ ይረዳል፡፡” የዐጀሚ ሥነ ጽሑፍ ቅርስ በተለይ የኅብረተሰቡን ባህላዊ ታሪክ ለሚያጠኑ ተመራማሪዎች ጥሩ መረጃ ሊሆን እንደሚችልም ተጠቁሟል፡፡
<>

Next >

No comments: